ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
በሩሲያ የክተት ጥሪ ተቃውሞ ምክንያት በመቶዎች የሚቆጠሩ ታሰሩ
ሩስያ ያሳለፈችውን አዲስ "ከፊል የክተት” አዋጅ በመላ ሃገሪቱ የተቃወሙ በመቶዎች የሚቆጠሩ ሰዎች መታሰራቸውን የገለልተኛ የመብት ተሟጋች ድርጅት አስታወቀ።
ኦቪዲ-ኢንፎ እንዳስታወቀው ቅዳሜ ዕለት ብቻ በ32 የተለያዩ ከተሞች 724 ሰዎች በቁጥጥር ስር ውለዋል።
ፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲን በዩክሬን የሚዋጉ 300 ሺህ ተዋጊዎችን ለመልመል ቀዳቸውን ካስታወቁ በኋላ መጠነ ሰፊ ተቃውሞዎች ተደርገዋል።
ፈቃድ ያላገኙ ሰልፎች በሩሲያ ህግ መሰረት ይታገዳሉ።
ፑቲን ሲቪሎችን ወደ ውትድርና ለማስገባት የወሰዱት እርምጃ በከተሞች አካባቢ ከፍተኛ ተቃውሞ ያስነሳ ሲሆን በዚህ ሳምንት መጀመሪያ ላይ በተደረጉ ሰልፎች ከ1 ሺህ በላይ ሰዎች ታስረዋል።
ኤኤፍፒ የዜና ወኪል አንዲት ሰልፈኛ ሞስኮ ውስጥ ስትታሰር “እኛ መድፍ አይደለንም" ስትል መመልከቷን ዘግቧል።
በሩሲያ ሁለተኛ ከተማ በሆነችው በሴንት ፒተርስበርግ አንድ ግለሰብ ለጋዜጠኞች “ለፑቲን ብዬ ወደ ጦርነት መሄድ አልፈልግም” ብሏል።
የሰባ ዓመቷ ናታሊያ ዱቦቫ ጦርነቱን እንደተቃወመች ገልጻ “ዝመቱ እንዳይባሉ ሰግቻለሁ” ብላለች።
ቅዳሜ ዕለት ከታሰሩት መካከል አንዳንዶቹ ወረቀት የተሰጣቸው ሲሆን ወደ ምልመላ ማዕከላት እንዲቀርቡ በጸጥታ ኃላፊዎች መታዘዛቸውን ተናግረዋል። ክሬምሊን በዚህ ሳምንት መጀመሪያ ላይ ድርጊቱን "ከህግ ጋር አይቃረንም" ሲል ውሳኔውን ተከላክሏል።
ውሳኔውን በሚቃወሙ ላይም ሞስኮ ከባድ አዲስ ቅጣትን አጽድቃለች።
እጁን ሲሰጥ፣ ወታደሩን ጥሎ ለመውጣት ሲሞክር ወይም ለመዋጋት ፈቃደኛ ባልሆነ በማንኛውም ወታደር ላይ እስከ 10 ዓመት የሚደርስ እስራት የሚያስቀጣ አዲስ ድንጋጌ መተላለፉን ፑቲን በፊርማቸው ቅዳሜ ዕለት አጽድቀዋል።
ፕሬዚዳንቱ በሃገሪቱወታደራዊ አባልነት ለአንድ ዓመት ለማገልገል ለሚመዘገብ ማንኛውም የውጭ ዜጋ የሩስያ ዜግነት እንዲሰጥም ፈርመዋል።
አንዳንድ ታዛቢዎች ይህ አዋጅ በሞስኮ ያለው የወታደር እጥረት ምን ያህል ከባድ እንደሆነ የሚያሳይ ነው ብለዋል።
በሌላ ዜና ደግሞ የክተት አዋጁን ተከትሎ ሩሲያውያን ወጣቶች ከሃገሪቱ ለመውጣት መሸሽ ቀጥለዋል።
ሃገሪቱን ከጆርጂያ ጋር በሚያዋስናት ድንበር የሩሲያ መኪኖች ወረፋ ከ 30 ኪ.ሜ በላይ ሆኗል።
በአካባቢው ያሉ የሩሲያ ባለስልጣናት ለመሻገር የሚሞክሩ ከፍተኛ መኪኖች መጉረፋቸውን አምነዋል። ወደ 2 ሺህ 500 የሚጠጉ መኪኖች በአንድ የፍተሻ ጣቢያ ብቻ ወረፋ እየጠበቁ ነው።
ሩሲያውን ወጣቶች እየሸሹ ነው የሚለውን ዘገባ ክሬምሊን ሐሙስ ዕለት “ሐሰት” ሲል ገልጿል።
ቢቢሲ በሩሲያ ድንበር ላይ ያነጋገረው አንድ ሰው በወረፋው ላይ ከመላው ሩሲያ የመጡ የመኪና ታርጋ ቁጥሮችን ማየት እንደሚቻል ተናግሯል።
ወደ ፊንላንድ ለመግባት የሚፈልጉ ሩሲያውያን ቁጥር በከፍተኛ ሁኔታ ጨምሯል ።
የሀገሪቱ የድንበር ጠባቃ ቃል አቀባይ ማቲ ፒትካኒቲ ካለፈው ሳምንት ጀምሮ ድንበር የደረሱት ሩሲያውያን ቁጥር በእጥፍ ጨምሯል ብለዋል።
አርብ ዕለት የሃገሪቱ መንግስት ወደ ሃገሪቱ የሚገቡትን የሩሲያ ቱሪስቶች ለማስቆም ማቀዱን አስታውቋል።
ሌሎች በርካታ አጎራባች ሃገሮችም ረቂቁን መሸሽ ለሚፈልጉ ሩሲያውያን ጥገኝነት እንደማይሰጡ ወስነዋል።