በታዳጊዋ ግድያ አባት፣ የእንጀራ እናት እና አጎት ክስ ተመሰረተባቸው

ታትሟል

በዩናይትድ ኪንግደም በ10 ዓመት ታዳጊ ልጅ ግድያ ወላጅ አባቷ፣ የእንጀራ እናቷ እና አጎቷ ክስ ተመሰረተባቸው።

በደቡብ ምስራቅ እንግሊዝ በምትገኘው ሰሪ ከተማ የ41 ዓመቱ ኡርፋን ሻሪፍ፣ እጮኛው ቤይናሽ ባቶል እና የኡርፋን ታናሽ ወንድም ፋይሰል ማሊክ በ10 ዓመቷ ታዳጊ ሳራ ሻሪፍ የግድያ ክስ እንደተመሰረተባቸው ፖሊስ አስታውቋል።

ሳራ ሻሪፍ የተባለችው ታዳጊ አስክሬን በምትኖርበት ቤት ነሐሴ 4/2015 ዓ.ም. ከተገኘ በኋላ የወንጀል ድርጊቱ አነጋጋሪ ሆኖ ቆይቷል።

በአስክሬን ላይ የተደረገ ምርመራ ታዳጊዋ “በርካታ እና ከባድ አካላዊ ጉዳት” ደርሶባት እንደነበረ አሳይቷል።

በግድያ ወንጀል የተከሰሱት ሦስቱ ግለሰቦች የታዳጊዋ አስክሬን ከመገኘቱ አንድ ቀን ቀደም ብሎ ማለትም ነሐሴ 3/2015 ዓ.ም. ወደ ፓኪስታን ተጉዘው ነበር።

ከዚያም ሦስቱ ግለሰቦች ከዱባይ ተነስተው ወደ ዩኬ ከመጡ በኋላ ለንደን ከተማ ዙሪያ በሚገኘው ጋትዊክ አየር ማረፊያ በቁጥጥር ሥር ውለዋል።

ፖሊስ ሦስቱ ግለሰቦች ላይ የወንጀል ክስ መመስረቱን እና ዛሬ ረፋድ ላይ ፍርድ ቤት እንደሚቀርቡ ይፋ አድርጓል።

ሦስቱ ግለሰቦች ነሐሴ 3 ላይ ወደ ፓኪስታን ሲያቀኑ የሟች ሳራ እህት እና ወንድም የሆኑ አምስት ልጆችን አስከትለው መሆኑን ፖሊስ ጨምሮ አስታውቋል።

ከአንድ እስከ 13 ዓመት የዕድሜ ክልል ውስጥ የሚገኙት ታዳጊዎች በፓኪስታን በአባታቸው አባት መኖሪያ ቤት የተገኙ ሲሆን ለደኅንነታቸው ሲባል በመንግሥት ወደሚተዳደር የሕጻናት ማቆያ ስፍራ እንዲዘዋወሩ ተደርጓል ተብሏል።

የዩኬ ፖሊስ ለሳራ ወላጅ እናት በባለሙያዎች የታገዘ አስፈላጊውን ድጋፍ እያደረኩ ነው ብሏል።