ሕንድ ውስጥ ሁለት የጦር አውሮፕላኖች አየር ላይ ተጋጭተው አንድ አብራሪ ሞተ

የፎቶው ባለመብት, Reuters
በማዕከላዊ ሕንድ ሁለት የአገሪቱ ጦር አየር ኃይል ተዋጊ ጀቶች አየር ላይ ተጋጨተው የአንደኛው ፓይለት ሕይወት አለፈ።
የጦር አውሮፕላኖች መደበኛውን የዘመቻ በረራ ሥልጠና እየወሰዱ ሳለ መጋጨታቸውን አየር ኃይሉ ባወጣው መግለጫ አመልክቷል።
አየር ላይ የተጋጩት የጦር አውሮፕላኖች ሁለቱም ጋዊሎር ከተባለ የአየር ኃይል ወታደራዊ ጦር ሰፈር ከተነሱ በኋላ ከስፍራው 30 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ ከሚገኝ ቦታ ላይ ነው ተጋጭተው የወደቁት።
አየር ኃይሉ ለአውሮፕላኖቹ መጋጨት ምክንያቱ እንዲጣራ አዟል።
የተጋጩት የጦር አውሮፕላኖች ሩሲያ ሰራሹ ሱክሆይ 30 የተሰኘ እና ሁለት ፓይለቶችን የያዘ እንዲሁም ሌላኛው ፈረንሳይ ሰራሽ የሆነ ሚራዥ 2000 የተባለ አንድ ፓይለት የያዘ የጦር አውሮፕላን ነው።
በተለያዩ አካባቢዎች የአውሮፕላኖች ስብርባሪዎች መገኘታቸውን የሕንድ መገናኛ ብዙኃን ዘግበዋል።
የአውሮፕላኖቹ ስብርባሪ ከተገኙባቸው ቦታዎች መካከል አንዱ በሆነው ዳሃርማንደር በተባለው አካባቢ የሚገኙ አንድ የፖሊስ መኮንን ለፈረንሳይ የዜና ወኪል አንድ ፓይለት ጫቃ ውስጥ ተጎድቶ በሕይወት መገኘቱን ገልጸዋል።
“የአንዱን አውሮፕላን አካል አግኝተናል” ያሉት መኮንኑ “የሌላኛውን አውሮፕላን ከዚህ አካባቢ ርቆ ወድቆ ሊሆን ይችላል። የሚያፈላልጉ ባለሙያዎች አሰማርተናል” ሲሉ ገልጸዋል።
የሁለቱ የጦር አውሮፕላኖች ግጭት በሕንድ አየር ኃይል ካጋጠሙት ተከታታይ አደጋዎች አንዱ ነው።
ባለፈው ዓመት ጥቅምት ወር ላይ በቻይና ድንበር አቅራቢያ አንድ ሄሊኮፕተር ተከስክሶ አምስት ወታደሮች ሞተዋል።
ከዚያ ቀደም ብሎ በፈረንጆች 2021 ታሚል ናዱ በተባለችው ግዛት የጦር ኃይሉ ሄሊኮፕተር ተከስክሶ ባስነሳው እሳት የሕንድ ጦር አዛዥ የነበሩት ጄኔራል ቢፒን ራዋትን ጨምሮ በርካታ ሰዎች ሞተዋል።












