ሩሲያ እና ምዕራባውያን ከቀዝቃዛው ጦርነት ማክተም ወዲህ ትልቅ የተባለ የእስረኞች ልውውጥ አደረጉ

የፎቶው ባለመብት, US government
በሩሲያ እና ምዕራባውያን መካከል ትልቅ የእስረኞች ልውውጥ ተካሂዶ ሦስት አሜሪካውያን ከሩሲያ ተለቀው አሜሪካ ገቡ።
ከሦስቱ አንደኛው የዋል ስትሪት ጆርናል ጋዜጠኛ ኢቫን ግሪሽኮቪች ነው። የ32 ዓመቱ ጋዜጠኛ በእስረኛ ልውውጥ ውስጥ ካሉት 16 እስረኞች መካከል አንዱ ሲሆን አሜሪካ በምላሹ ስምንት ሩሲያውያን እስረኞችን ትለቃለች።
ከቀዝቃዛው ጦርነት ማክተም በኋላ በሩሲያና ምዕራቡ ዓለም ትልቁ የእስረኞች ልውውጥ ተብሏል።
በቱርክ አየር ኃይል በተደረገው ልውውጥ ነጻ ከወጡ መካከል የቀድሞው የአሜሪካ ባሕር ኃይል ፓል ዌን እና ሩሲያዊ-አሜሪካዊ ጋዜጠኛ አልሱ ኩርማሺቫ ይገኙበታል።
አሜሪካ፣ ሜሪላንድ ሲደርሱ በከፍተኛ ደስታ ተሞልተው ነበር።
ፕሬዝዳንት ጆ ባይደን እና ምክትል ፕሬዝዳንት ካማላ ሀሪስ አቀባበል አድርገውላቸዋል። ከቤተሰቦቻቸው ጋርም ተገናኝተዋል።
ባይደን ከመለቀቃቸው በፊት “ያሉበት ክፉ ሁኔታ አክትሟል” ብለዋል።

የፎቶው ባለመብት, Reuters
የአሜሪካ አጋሮች ጀርመን እና ስሎቬንያ ለተጫወቱት ሚና አመስግነዋቸዋል።
ዋነኛ የክሬምሊን ተቃዋሚ ቭላድሚር ካራ-ሙራዝ ከተፈቱት መካከል ይጠቀሳል።
መለቀቃቸው “የዲፕሎማሲ ውጤት” ተብሏል።
የተለቀቁት ሦስት አሜሪካውያን ለጤና ምርመራ ወደ ቴክሳስ ይወሰዳሉ።
የእስረኞች ልውውጥ ድርድሩ ከ18 ወራት በላይ ወስዷል።
ሩሲያ ካስለቀቀቻቸው መካከል ቫዲም ክራስኮቭ ይገኝበታል።
በጀርመን፣ በርሊን ፓርክ ውስጥ ግድያ በመፈፀም የዕድሜ ልክ እስራት ተፈርዶበት የነበረ ሲሆን፣ አሁን ወደ ሩሲያ ተመልሷል።
ከእስር የተለቀቀው ክራስኮቭ የሩሲያ ደኅንነት ሠራተኛ ሲሆን የቀድሞ የቸቸን አማጺያን ኮማንደርን እንዲሁም ለስሎቬንያ በመሰለል ጥፋተኛ የተባሉ ሩሲያውያን ጥንዶችን በመግደል ነበር ጀርመን ውስጥ ታስሮ የነበረው።

የፎቶው ባለመብት, Reuters
በቱርክ አጠቃላይ የእስረኞች ልውውጥ የተደረገው ለ26 ሰዎች ነው።
እስረኞቹ ከአሜሪካ፣ ጀርመን፣ ፖላንድ፣ ስሎቬንያ፣ ኖርዌይ፣ ሩሲያ እና ቤላሩስ ናቸው።
ሁለት ታዳጊዎችን ጨምሮ 10 ሰዎች ወደ ሩሲያ ሲመለሱ፣ 13 እስረኞች ወደ ጀርመን፣ ሦስት እስረኞች ወደ አሜሪካ ተመልሰዋል።
ፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲን ከእስር የተለቀቁትን የአበባ ጉንጉን አዘጋጅተው በሞስኮ አውሮፕላን ማረፊያ ተቀብለዋቸዋል።
ፑቲን እስረኞቹን በደማቅ ሁኔታ ተቀብለው፣ አቅፈው በቀይ ምንጣፍ ላይ አብረዋቸው ተጉዘዋል።
በሩሲያ አሸማጋይነት የተደረገውን የእስረኞች ልውውጥ፣ የሰሜን አትላንቲክ ጦር ቃልኪዳን (ኔቶ) እና የአውሮፓ ኅብረት ደግፈውታል።












