የቀድሞ የአልሸባብ መሪ ሚንስትር ሆነው ተሾሙ

ታትሟል

የአልሻባብ ሁለተኛ ሰው የነበሩት ሙክታር ሮቦው በሶማሊያ ሚንስትር ሆነው ተሾሙ።

በአዲሱ የሶማሊያ ፕሬዝዳንት ሐሰን ሼይክ ሞሐሙደ አስተዳደር ውስጥ ሚንስትር ሆነው እንዲያገለግሉ የተሾሙት ሮቦው፤ የአልሻባብ ቃል አቀባይ ሆነውም አገልግለዋል።

በ2018 በቁጥጥር ስር ከዋሉ በኋላ በቀድሞ አስተዳደር ስር በቁም እስር ላይ ቆይተዋል።

አቡ መንሱር በመባልም የሚታወቁት ሙክታር ሮቦው፤  እአአ ነሐሴ 2017 ለሶማሊያ መንግሥት እጃቸውን ሰጥተው ነበር።

ይህም ከአልሻባብ የከዱ ከፍተኛው አባል አድርጓቸዋል።

በታህሳስ 2018 በሶማሊያ ለደቡብ ምዕራብ ክልል አስተዳዳሪነት የምርጫ ዘመቻ ሲያደርጉ ታስረው ለቁም እስር ተዳርገው ነበር።

በወቅቱ በቁጥጥር ስር መዋላቸውን አስመልክቶ መንግሥት ባወጣው መግለጫ፤ ሮቦው በባይዶዋ ሚሊሻዎችን ሲያደራጁ ነበር ብሏል።

የወቅቱ የሶማሊያ መንግሥት ሮቦው ከጽንፈኛ አመለካከታቸው አልተላቀቁም የሚል ክስ አቅርቦባቸው ነበር። መታሰራቸውን ተከትሎ በተፈጠረ ግጭት ከ20 በላይ ሰዎች ተገድለዋል።

ሙክታር ሮቦው የርዕዮተ ዓለም ልዩነትን በመጥቀስ ከአልሻባብ መውጣታቸውን በ2015 አስታውቀዋል።

በኋላም ቡድኑን የሚዋጋ የራሳቸውን ቡድን አቋቁመዋል።

እአአ ሰኔ 2017 የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ መስሪያ ቤት በአልቃይዳ የሰለጠኑትን ታጣቂ ከሽብር መዝገቡ ውስጥ ፍቋል። ያሉበትን ለጠቆመ ሰው ሊሰጥ የነበረውን አምስት ሚሊዮን ዶላርም አንስቷል።

አሁን ሮቦው የኃይማኖት ጉዳዮች ሚኒስትር በመሆን ተሹመዋል።

አንዳንዶች ይህ በአልሻባብ ላይ የርዕዮተ ዓለም ጦርነት ማወጅ ሊሆን ይችላል ቢሉም ሌሎች ደግሞ የአል-ቃኢዳ ተባባሪ በሆነው ቡድን አመራር ሆነው ሳለ በእሳቸው ስር ለተፈጸሙ ወንጀሎች መሸፈኛ አድርገውም ይመለከቱታል።

አልሻባብ በሶማሊያ፣ በኬንያ እና በሌሎች የምስራቅ አፍሪካ አካባቢዎች ጠቃቶችን ይሰነዝራል።