ኢራቅ ለ300 ሰዎች ሞት ምክንያት ነበሩ ያለቻቸውን ሦስት ሰዎች በስቅላት ቀጣች

ታትሟል

ኢራቅ በፈረንጆቹ 2016 ዓ/ም በባግዳድ ቦምብ በማፈንዳት 300 ሰዎችን ገድለዋል ያለቻቸው ሦስት ሰዎች በስቅላት ቀጣች።

ይህ የቦምብ ጥቃት ከአሜሪካ መራሹ ወረራ ወዲህ ብዙ ሰዎች የተገደሉበት ነበር ተብሏል።

በወቅቱ የኢስላሚክ ስቴት (አይኤስ) ለጥቃቱ ኃላፊነት ወስዶ ነበር።

የጠቅላይ ሚኒስትር ሞሐመድ ሺያ አል ሱዳኒ ቢሮ ይህን ጥቃት ፈጽመው በስቅላት የተቀጡትን ሰዎች ማንነት በስም ይፋ አላደረገም። ይሁንና ስቅላቱ ከትናንት በስቲያ እሑድ እና ትናንት ሰኞ መፈጸሙ ተዘግቧል።

አንድ መንግሥታዊ ምንጭ ለኤኤፍፒ የዜና ወኪል በሰጡት ፍንጭ ግን የአይኤስ አባልና ዋንኛ የጥቃቱ አቀናባሪ ጋዝዋን አል ዘውባኢ በስቅላት ከተቀጡት ሦስት ሰዎች አንዱ ነው።

ጋዝዋን አል ዛውቢ በቁጥጥር ሥር ውሎ ወደ ኢራቅ ተላልፎ የተሰጠው በፈረንጆቹ 2021 ዓ/ም ነበር።

በፈረንጆቹ አቆጣጠር በሐምሌ፣ 2016 ዓ/ም በበርካታ ተቀጣጣይ የተጠመዱ ቦምቦች የታጨቀ አንድ ተሽከርካሪ በርካታ ሰዎች በሚገበያዩበትና በርካታ የሺአ ሙስሊሞች በሚገኙበት የካራዳ ገበያ ላይ ፈንድቶ ነው 300 ኢራቃዊያን የሞቱት።

በወቅቱ የረመዳን ጾም ወቅት የነበረ ሲሆን ምእመናን ከኢፍጣር በኋላ ሰብሰብ ብለው ግብይት በሚያከናውኑበት ገበያ ነበር ጥቃቱ የተፈጸመው።

በርካታ ሰዎች የሞቱት በቀጥታ በቦንቡ ፍንጣሪ ሳይሆን ፍንዳታውን ተከትሎ ገበያ ማዕከሉ በእሳት በመያያዙ ብዙ ሰዎችን እሳት በልቷቸው ነው።

ይህን ጥቃት ተከትሎ የአገር ውስጥ ሚኒስትሩ ሞሐመድ ጋባን በገዛ ፈቃዳቸው ሥልጣን መልቀቃቸው ይታወሳል።

በወቅቱ ጠቅላይ ሚኒስትር የነበሩት ሙስጠፋ አልካዲሚ ከጥቃቱ ጀርባ ያለው ሰው ጋዝዋን አል ዛውባኢ እንደሆነ ተናግረው ነበር።

አይ ኤስ የተሰኘው አክራሪ ቡድን 88ሺህ ስኳር ካሬ የሚደርስና ከኢራቅ እስከ ሲሪያ የሚደርስ ግዛትን በቁጥጥሩ ሥር አድርጎ በሚያስተዳድርበት ወቅት ስምንት ሚሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎች ለብዙ ስቃይና መከራ ተዳርገዋል።

ቡድኑ በፈረንጆቹ 2017 ዓ/ም በኢራቅ ቢሸነፍም፣ ከሁለት ዓመት በኋላ ደግሞ በሶሪያ ተመሳሳይ ሽንፈት ቢገጥመውም በሁለቱም አገራት በርካታ ሚሊሻዎች እንዳሉት ይነገራል።

የተባበሩት መንግሥታት አይ ኤስ እስከ ሰባት ሺህ ሚሊሻዎች እንዳሉት ይገመታል።