የኬንያ የፖሊስ ኃላፊ በጦማሪው ግድያ ታሰሩ

የፎቶው ባለመብት, AFP via Getty Images
በኬንያ መዲና ናይሮቢ የሚገኝ ዋና ፖሊስ ጣቢያ ኃላፊ በፖሊስ ቁጥጥር ሥር ሳለ ከተገደለው ወጣት ጦማሪ ጋር በተያያዘ መታሰራቸውን ገለልተኛ መርማሪዎች ገለጹ።
ከጣቢያው አዛዥ ሳምሶን ታላም በተጨማሪም የፖሊስ መኮንኑ ጀምስ ሙክዋን እና የፖሊስ ጣቢያውን የደኅንነት ካሜራ በማጥፋት የተከሰሱ ቴክኒሽያን በቁጥጥር ሥር ውለዋል።
ፖሊስ ጦማሪው አልበርት ኦጂዋንግ የሞተው ጭንቅላቱን ግድግዳ ጋር በማጋጨት ራሱ ላይ ጉዳት በማድረስ ነው ያለ ቢሆንም ይህ በሐኪሞች ውድቅ ከተደረገ በኋላ ሰፊ ቁጣ ተቀስቅሷል።
ሐኪሞች አልበርት ሕይወቱ ያለፈው በደረሰበት ጥቃት ምክንያት እንደሚሆን ድምዳሜ ላይ ደርሰዋል።
በጉዳዩ ላይ ገለልተኛ ምርመራ መካሄዱን ተከትሎም ቢያንስ በ23 ሰዎች ላይ ምርመራ የተካሄደ ሲሆን ሌሎች አምስት ሰዎችም ከመደበኛ ሥራቸው ተነስተዋል።
የ31 ዓመቱ ኦጅዋንግ በፖሊስ ቁጥጥር ሥር ሳለ ሕይወቱ ያለፈው ባለፈው ሳምንት መጨረሻ ነበር።
ጦማሪው በፖሊስ የተያዘው በኤክስ ገጹ ላይ በምክትል ኢንስፔክተር ኢሊዩድ ላጋት ላይ ትችት መጻፉን ተከትሎ ነበር።
ፖሊስ መጀመሪያ ላይ በሰጠው መግለጫ ኦጅዋንግ በእስር ቤት ክፍሉ ራሱን ስቶ እንደተገኘ እና በከተማዋ ወደሚገኝ ሆስፒታል መወሰዱን ጠቅሶ፣ ግድግዳ ጋር ጭንቅላቱን በማጋጨቱ ሕይወቱ ሊያልፍ እንደቻለ ገልጿል።
ሆኖም የአስክሬን ምርመራ ውጤት እና ፖሊስን በገለልተኝነት በሚቆጣጠረው ገለልተኛው የፖሊስ ታዛቢ ባለሥልጣን (አይፒኦኤ) ባካሄደው ምርመራ ኦጅዋንግ ራሱን ገድሎ ሊሆን ይችላል የሚለውን የፖሊስ ገለጻ ውድቅ አድርጎታል።
ኢንስፔክተር ዳግላስ ካንጃም ቀደም ሲል የሰጡትን መግለጫ የሻሩ ሲሆን በሰራተኞቻቸው የተፈጠረ "የተሳሳተ መረጃ" መሆኑን በመግለጽ ይቅርታ ጠይቀዋል።
አርብ ዕለት ሙክህዋና ፍርድ ቤት የቀረቡ ሲሆን የዋስትና ችሎት እስከሚሰማበት አንድ ሳምንት ጊዜ ድረስ በእስር ላይ ይገኛሉ።
በወንጀል መርማሪዎች ለፍርድ ቤት የቀረቡ የመጀመሪያ ደረጃ የምርመራ ውጤቶች ሙክሀዋና እና ሌሎች ተጠርጣሪዎች የደኅንነት ካሜሪያዎችን ማጥፋትን ጨምሮ በኦጅዋንግ ግድያ ሴራ ላይ ተሳትፎ እንዳላቸው አመልክተዋል።
ሙክህዋና የቀረበባቸውን ክስ በተመለከተ እስካሁን ምላሽ አልሰጡም። ሆኖም ጠበቃቸው ኮንስታብሉ በተጠሩ ጊዜ ራሳቸውን ማቅረባቸውን በመጥቀስ ዋስትና እንዲሰጣቸው ጠይቀዋል።
ሐሙስ ዕለት የጦማሪው ግድያ ያስቆጣቸው በመቶዎች የሚቆጠሩ ተቃዋሚዎች አደባባይ በመውጣት ምክትል ኢንስፔክተር ላጋት ከኃላፊነታቸው እንዲለቁ ጠይቀዋል።
ጀኔራል ላጋት ከኃላፊነታቸው እንዲለቁ አሊያም እንዲታገዱ ከሕዝብ፣ ከተቃዋሚ ፓርቲ መሪዎች እና ከሲቪል ማሕበረሰብ ቡድኖች ከፍተኛ ጫና ደርሶባቸዋል።
ፕሬዚደንት ዊሊያም ሩቶም አፋጣኝ ምርመራ እንዲደረግ የጠየቁ ሲሆን አስተዳደራቸው ዜጎችን ከሕገ ወጥ ፖሊሶች እንደሚጠብቅ አርብ ዕለት ቃል ገብተዋል።
ፕሬዚደንቱ ከሦስት ዓመት በፊት ወደ ሥልጣን ሲመጡ ከፖሊስ የጭካኔ ተግባር እና ካለ ፍርድ ግድያ ጋር ተያይዞ የሚነሳው የኬንያ ታሪክ እንዲያከትም እንደሚያደርጉ ቃል ገብተው ነበር።
ሆኖም በኬንያ ባለፈው ዓመት ብቻ ወደ 160 የሚጠጉ ያለፍርድ ግድያዎች እና አስገድዶ መሰወሮች እንደተፈፀሙ የአገሪቱ የሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን ገልጿል።
ገለልተኛ የሆነው የፖሊስ ተቆጣጣሪ ተቋምም ባለፉት አራት ወራት ብቻ ቢያንስ 20 ሰዎች በፖሊስ ከተያዙ በኋላ ተገድለዋል ብሏል።















