'ከውድቀት' እስከ አፍሪካ ኮከብነት የዘለቀው የሉክማን አስገራሚ ጉዞ

ታትሟል
የንባብ ጊዜ: 3 ደቂቃ

"ለአፍሪካ ወጣቶች መናገር የምፈልገው፡ ተስፋ አትቁረጡ። ህመምን ወደ ድል ለውጡ የሚለውን ነው።"

አዴሞላ ሉክማን የአፍሪካ ኮከብ ተጫዋች ሆኖ እኪመረጥ ድረስ በርካታ ውጣ ውረዶችን አልፏል። ናይጄሪያዊው አሁን እያስመዘገበ የሚገኘው ስኬት ለብዙዎች መነሳሻ የሚሆን ነው።

ገና በለጋ ዕድሜው በከፍተኛ የዝውውር ገንዘብ ወደ እንግሊዝ ፕሪሚየር ሊግ ያደረገው ጉዞ ስኬታማ አልነበረም። በበርካታ ክለቦችም በውሰት ለማሳለፍ ተገዷል። ስኬትን ማጣጣም የጀመረው ግን ወደ ጣሊያን ተጉዞ እአአ በ2022 አትላንታን በተቀላቀለ ማግስት ነው።

"ከአራት ዓመት በፊት የእግር ኳስ ህይወቴ አጣብቂኝ ውስጥ ገብቶ ነበር። ዛሬ ደግሞ አፍሪካ ኮከብ ተብዬ ሽልማቴን ለመቀበል በቅቻለሁ" ሲል የ27 ዓመቱ ተጫዋች ሽልማቱን ማራካሽ ተገኝቶ ሲቀበል ተናግሯል።

"እንቅፋቶች ህልማችሁን ከማሳካት ሊገቷችሁ አይገባም።"

ቢቢሲ አፍሪካ ስፖርት የአፍሪካ ኮከብ ተጫዋች በመሆን ከራሺዲ የኪኒ፣ ቪክተር ኢክፔባ፣ ኢማኑኤል አሙኒኪ፣ ንዋንክዎ ካኑ እና ቪክተር ኦሲሜህን ቀጥሎ ስድስተኛው ናይጄሪያዊ የሆነውን ሉክማንን ጉዞ እንደሚከተለው ቃኝቶታል።

የልጅነት ጉዞ

ከናይጄሪያውን ወላጆች በደቡበ ለንደን ተወለደ። ከልጅነቱ ጀምሮ ለእግር ኳስ ጥልቅ ፍቅር ነበረው።

"ካልሲዎቼን ጠቅልዬ ቤት ውስጥ ስጫወትባቸው አስታውሳለሁ" ሲል ለቢቢሲ ስፖርት ተናግሯል።

በእንግሊዝ ሁለተኛው ሊግ ለሚጫወተው ቻርልተን አትሌቲክ ፈረመ። በ2014 የየሁለተኛ ደረጃ መልቀቂያ ፈተናውን አለፈ።

"እናቴ ለትምህርት ትኩረት ትሰጣለች። ናይጄሪያዊ ስትሆን ደግሞ ጉዳዩ ይበልጥ ጠንከር ይላል። ተጽዕኖው ከባድ ነበር" ብሏል።

ሉክማን ለቻርልተን ዋናው ቡድን እአአ በ2015 ተሰለፈ። በአምስተኛ ጨዋታው ደግሞ ጎል አስቆጠረ። እየተንገዳደገደ በሚገኘው ክለብ ውስጥ ያሳየው እንቅስቃሴ የታላላቅ ቡድኖችን ቀልብ ሳበ።

በ2017 ኤቨርተን የ19 ዓመቱን ሉክማንን በ11 ሚሊዮን ፓውንድ አስፈረመው። በወቅቱ የክለቡ አሰልጣኝ ሮናልድ ኩማን "የወደፊቱ ኮከብ ተጫዋች" ተብሎ አሞካሸው።

"ከወጣቱ ብዙ እንጠብቃለን። በደንብ ከሰለጠነ እና ከተሻሻለ ከፍተኛ ደረጃ ላይ እንደሚደርስ አስባለሁ" ሲሉ ሆላንዳዊው አሰልጣኝ ተናገሩ።

ተቀይሮ በገባበት በመጀመሪያ ጨዋታው ጎል አስቆጠረ፤ ቡድኑም ማንቸስተር ሲቲን 4 ለምንም አሸነፈ። ውጤታማነቱ ግን አልቀጠለም።

አንደኛው ምክንያት በክለቡ የተቀያየሩት የአስልጣኞች ጉዳይ ነው። በኤቨርተን በቆየባቸው ሁለት ከግማሽ ዓመታት ስድስት አሰልጣኞች (ጊዜያዊዎቹን ጨምሮ) ተፈራርቀዋል።

አዲስ ጅማሮ

ሉክማን እአአ በ2017 በተካሄደው ከ20 ዓመት በታች የዓለም ዋንጫ እንግሊዝ ባለድል እንድትሆን አግዟል። በደቡብ ኮሪያ በተዘጋጀው ውድድር ላይ ሦስት ጎሎችን አስቆጥሯል።

በ2018 በውሰት ወደ አርቢ ሊፕዢግ በማቅናት ውጤታማ ስድስት ወራትን አሳለፈ። በ22.5 ሚሊዮን ፓውንድ ለጀርመኑ ክለብ በመፈረም ዝውውሩ ቋሚ ተደረገ።

ዝውውሩ ቋሚ በተደረገበት የውድድር ዓመት ግን ለክለቡ አንድ ጊዜ ብቻ በቋሚነት ለመሰለፍ በቃ።

በቀጣዮቹ የውድር ዓመታት ወደ ፕሪሚየር ሊግ በመመለስ በውሰት ለፉልሃም እና ሌስተር ተጫወተ።

የሌስተር የወቅቱ አሰልጣኝ የነበሩት ብሬንዳን ሮጀርስ የሰጡት አስተያየት ሉክማን በልምምድ ስፍራ ጠንክሮ እየሰራ መሆኑን ነው። በቋሚነት ለመሰለፍ ግን በቂ ዕድል ማግኘት አልቻለም።

"ሌሎች ተጫዋቾች ከሄዱ በኋላ ወደ ኋላ ቀርቶ በሁለቱም እግሮቹ ይለማመዳል" ብለዋል ሮጀርስ።

ራሱን ያሻሻለው ተጫዋች

ናይጄሪያ ተጫዋቹን በብሔራዊ ቡድኗ ውስጥ ላማካተት ተደጋጋሚ ሙከራ አድርጋለች። በ2021 ሉክማን ተስማማ።

ለብሔራዊ ቡድኑ ባደረገው ሁለተኛ ጨዋታ ናይጄሪያ በጥሎ ማለፍ ቸዋታ በጋና ተሸንፋ ከ2022 የዓለም ዋንጫ ውጭ ሆነች።

ቀጣይ ማረፊያው የቤርጋሞው አታላንታ ሆነ።

"መጀመሪያ ስፈርም ምግብ ቤት ሄጄ እራት በላሁ። ደስ ሚል ምሽት ነበር" ሲል ያቺን ምሽት አስታውሷል።

በሎምባርዲ ያለው ህይወት ዘና ያለ ነው። በማጥቃት ላይ የተመሰረተ አጨዋወት ለሚመርጠው አትላንታ ሉክማን ደግሞ ሜዳ ላይ ድንቅ መሆኑን ማስመስከር ያዘ።

97 ጨዋታዎችን ለክለቡ በማድረግ 43 ጎሎችን አስቆጠረ። 23 ለጎል የሚሆኑ ኳሶችን አቀብሏል።

ከእነዚህ ጎሎቹ ውስጥ ሦስቱን ያስቆጠረው አትላንታ በአውሮፓ መድረክ የመጀመሪያውን ድል ባመስዘገበበት የዩሮፓ ሊግ የዋንጫ ጨዋታ ዕለት ነበር። በአውሮፓ መድረክ በተደረገ የፍጻሜ ጨዋታ ሃትሪክ በመስራትም ከ49 ዓመታት በኋላ የመጀመሪያው ተጫዋች ለመሆን በቅቷል።

የናይጄሪያዎች ተስፋ

ሉክማን አሁን ለብሔራዊ ቡድኑም ሆነ ለክለቡ ቋሚ ተሰላፊ ሆኗል። በ2023ቱ የአፍሪካ ዋንጫ ናይጄሪያ እስከፍጻሜ ስትጓዝ ቡድኑ ቁልፍ ተጫዋች መሆኑን አስመስክሯል።

በውድድሩ ላይ ካሜሮንን ሲያሽንፉ ሁለት ጎሎችን ከማስቆጠሩም በላይ በሩብ ፍጻሜው አንጎላ ላይ የማሸነፊያዋን ጎል ከመረብ አገናኝቷል።

ብሔራዊ ቡድኑ ሁለተኛ ሆኖ ቢያጠናቅቅም ሉክማን የውድድሩ ምርጥ ቡድን ውስጥ ለመከታተት በቅቷል።

"ድንቅ ተሰትኦ" ከማለት ባለፈ የአፍሪካ ኮከብ ተጫዋች ሊሆን እንደሚገባው የብሔራዊ ቡድን አጋሩ አሌክ ኢዎቢ ተናግሯል።

"ለውጡን ስላየን በስኬቱ አልተገረምንም" ሲልም ኢዎቢ ለቢቢሲ አስረድቷል።

"ውጤታማ ነው። ለሌሎች ተጫዋቾችም መነሳሳትን ይፈጥራል።"

"ወንድማችን በርትቶ ከሠራ እኛም ከእሱ እኩል ወይም ከእሱ በላይ መሥራት ይኖርብናል።"

ሉክማን በዘንድሮው የባለንዶር ዕጩዎች ውስጥ መካከተት የቻለ ብቸኛው አፍሪካዊ ነው። 14ኛ ሆኖ ለማጠናቀቅም ችሏል።

ባለፉት 12 ወራት ስላስመዘገበው መሻሻል ከቢቢሲ ስፖርት አፍሪካ ጥያቄ ቀርቦለት ነበር።

"ለውጤ ለማስበው ስኬት የመጀመሪያው እርምጃ ነው" ሲል መልሷል።

አትላንታ ሴሪአውን እየመራ ሲሆን የሉክማን ተጽዕኖም ከዕለት ወደ ዕለት እየጨመረ ነው።

ለዘንድሮው የአፍሪካ ኮከብ ተጫዋች በፕሪሚየር ሊጉ ያሳለፋቸው እነዚያ ከባድ ዓመታት ከተረሱ ሰነባብተዋል።