የአውሮፓ ኅብረት ኤርትራ በትግራይ ላይ ከፍታዋለች የተባለውን ጥቃት ወቀሰ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
የኤርትራ ወታደሮች ወደ ትግራይ ገብተው ጥቃት ከፍተዋል የሚሉ ሪፖርቶችን ተከትሎ ያለውን ጦርነት የበለጠ ያባብሰዋል ሲል የአውሮፓ ኅብረት አሳሰበ።
“የአውሮፓ ኅብረት ሁሉም ወገኖች ማንኛውንም ወታደራዊ መፍትሄ ወደጎን አድርገው ለሕዝቦቻቸው ጥቅም ሲሉ ወደ ሰላም ጥረቱ እንዲመለሱ በድጋሚ ያሳስባል” ሲሉ የኅብረቱ የውጭ ጉዳይ እና የደኅንነት ፖሊሲ ከፍተኛ ተወካይና የአውሮፓ ኮሚሽን ምክትል ፕሬዚዳንት ጆሴፍ ቦሬል ተናግረዋል።
የትግራይ ኃይሎች በኤርትራ ወታደሮች መጠነ ሰፊ ጥቃት እንደተከፈተባቸውና ከባድ ውጊያ ከኤርትራ ጋር በሚያዋስኗቸው አካባቢዎች መካሄዳቸውን ከሰሞኑ ተናግረዋል።
የኤርትራ ጦር ከተከዜ እስከ ኢሮብ ባለው በሁሉም ግንባሮች መጠነ ሰፊ ጥቃት እንደከፈቱ የተናገሩት የህወሓት ቃል አቀባይ አቶ ጌታቸው ረዳ፣ በተጨማሪም የኢትዮጵያ መከላከያ እና የአማራ ኃይሎችም ተሳትፈዋል ሲሉ ከስሰዋል።
ይህንን በተመለከተ ከኢትዮጵያም ሆነ ከኤርትራ መንግሥት አስካሁን የተባለ ነገር የለም።
በኢትዮጵያ ያለውን የእርስ በርስ ጦርነት በሰላም ለመቋጨት እየሞከሩ ያሉት የአፍሪካ ቀንድ የአሜሪካ ልዩ መልዕተኛ ማይክ ሐመር የኤርትራ ወታደሮች ድንበር አቋርጠው ወደ ትግራይ ክልል መግባታቸውን አሜሪካ ታውቃለች ብለዋል።
ማይክ ሐመር “የኤርትራ ጦር ከድንበር ማዶ የሚያደርጋቸውን እንቅስቃሴዎች ስንከታተል ቆይተናል” ካሉ በኋላ ይህንኑ የኤርትራ እንቅስቃሴ አገራቸው እንደምታወግዝ ተናግረዋል።
ለለሰብአዊ እርዳታ አቅርቦት አመቺነት ሲባል በተፋላሚ ወገኖች መካከል ተደርሶ የነበረው የተኩስ አቁም ባለፈው ነሐሴ ወር አጋማሽ ላይ ከፈረሰ በኋላ በተለያዩ አካባቢዎች ውጊያ መገርሸቱ ሲነገር ቆይቷል።
የኢትዮጵያ መንግሥት እና የትግራይ ኃይሎች ጋብ ብሎ ለነበረው ጦርነት እንደ አዲስ መቀስቀስ አንዳቸው ሌላኛቸውን ይከሳሉ።
ሁለት ዓመታት ሊሞላው ጥቂት ሳምንታት በቀረው የእርስ በርስ ጦርነት ኤርትራ ከኢትዮጵያ መንግሥት ጋር በመተበባር ከትግራይ ኃይሎቸ ጋር ስትዋጋ ቆይታለች።
በ2013 ዓ.ም. ጥቅምት ወር መጨረሻ ላይ ትግራይ ውስጥ ተከስቶ ወደ አማራና አፋር ክልሎች የተዛመተው ደም አፋሳሽ ጦርነት የአስር ሺዎችን ሕይወት በመቅጠፍ፣ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ዜጎችን በማፈናቀል መጠነ ሰፊ ሰብአዊ ቀውስ አስከትሏል።












