ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
የሰው ልጅ ትኋንን ማጥፋት ያልቻለበት ምክንያቱ ምንድነው?
ለትኋን ማጥፊያ ፍቱን መድኃኒት አለን የሚሉት ከሽያጩ የሚያተርፉት ብቻ ናቸው።
ትኋን በቀላሉ አይጠፋም። በቅርቡ የዓለም ቱሪስቶች መናኽሪያ የሆነችው የፈረንሳይዋ ዋና ከተማ ፓሪስ ራስ ምታት ሆኖ ነበር።
በሚሊዮን ዶላር ገንዘብ ከስክሳ ነው መቆጣጠር የቻለችው።
በፓሪስ ድንገት ትኋኖች ወረራ ፈጸሙ። ሆስፒታል አልቀራቸውም፤ ትምህርት ቤቶች፣ ሲኒማ ቤቶች ባቡሮች በትኋኖች ተወረሩ።
በውበቷ የምትመካው ፓሪስ፣ ኦሊምፒክ ለማሰናዳት ደፋ ቀና ትል የነበረችው ፓሪስ በትኋን ወረራ አንገቷን ደፋች።
በ2020 (እአአ) በፈረንሳይ አንድ ሆስፒታል በትኋን በመወረሩ እንዳለ መዘጋት ነበረበት። አንድ ታማሚ ነው ወደ ሆስፒታሉ ትኋን ይዞ ገባ ተብሏል።
የሰለጠኑ ውሾች ትኋኖቹ አራት ክፍሎችን እንደወረሩ አጋለጡ።
የሆስፒታሉ አንድ ክፍል ለ24 ቀናት መዘጋት ነበረበት። ትኋኖቹን ከዚያ ለመደምሰስ 400 ሺህ ዶላር ወጪ አስወጥቷል።
በዓለም ዙሪያ አሁን የትኋን ወረራ የማይናቅ ስጋት ሆኗል።
አየር መንገዶች መንገደኞች በሻንጣዎቻቸው ትኋን ይዘው እንዳይመጡባቸው ጥንቃቄ ማድረግ ይዘዋል።
አሁን ሳይቲስቶችን እያመራመረ ያለው አንድ ጥያቄ “ለምን ትኋን ማጥፋት እንዲህ ከባድ ሆነ?” የሚል ነው።
ትኋኖች የሚራቡት መቼ ነው?
ትኋኖች ሰዎች ጭልጥ ያለ እንቅልፍ እንደወሰዳቸው ሲረዱ ነው ለሥራ ከጎሬያቸው የሚወጡት።
ሳይንቲስቶች እንደሚሉት ትኋኖች ንቁ የሚሆኑት ሌሊት ለ5 ሰዓታት ነው። ይህም ከእኩለ ሌሊት ጀምሮ እስከ ማለዳ 11፡00 ሰዓት ነው። ይህ በአጋጣሚ የሆነ አይደለም።
ሰዎች ከእንቅስቃሴ የሚታቀቡበት ሰዓት ስለሆነ ነው።
ትኋኖችን ሁለት ነገር አቅጣጫ ይሰጣቸዋል።
አንዱ የሰው ሙቀት ሲሆን፣ ሁለተኛው ደግሞ ካርቦንዳይኦክሳይድ ነው። የሰው ሙቀትን ከአንድ ሜትር ርቀት ያህል ለይተው እንቅስቃሴ አለመኖሩን አውቀው ይጣበቃሉ።
ትኋኖችን ማጥፋት ለምን ፈታኝ ሆነ?
በኖርዝ ካሮላይና ዩኒቨርስቲ ተመራማሪ የሆኑት ዋረን በዝ በ2005 አንድ ጥናት ጀመሩ። የፀረ ተባይ መድኃኒት አምራቾችን አንድ ውለታ ጠየቁ። ከተለያዩ የትኋን ዝርያዎች ናሙና እንዲልኩላቸው አደረጉ።
ከ2005 - 2009 (እአአ) ድረስ 161 የትኋን ዘርያዎችን ከአሜሪካ መሰብሰብ ቻሉ።
ይህ ምርምራቸው በመሀል ከተቋረጠ ከዓመታት በኋላ በአዲስ መልክ ወደ 233 የትኋን ዓይነቶች ሰብስበው ዘረ መላቸውን (DNA) ማጥናት ጀመሩ።
አንድ የደረሱበት ውጤት ያሳያቸው ነገር ቢኖር ከሁለተኛው የዓለም ጦርነት ወዲህ ዲዲቲ በስፋት መረጨት ከጀመረ አንስቶ በርካታ የትኋን ዝርያዎች ፀረ ተባይ የሚባሉን ብዙዎቹን መድኃኒቶች መቋቋም መቻላቸውን ነው።
በ2016 በአውስትራሊያ የተደረገ ሌላ ጥናት ደግሞ ትኋኖች ቆዳቸው እየደደረ ፀረ ተባይ መድኃኒቶችን በዓመታት ውስጥ ይበጥል እየተቋቋሙ መምጣታቸውን ያስረዳል።
ሌላው ጥናት እንዳስረዳው ትኋኖች ፀረ ተባይ ከተረጨበት ቦታ ራሳቸውን በማራቅ፣ ከንክኪ በማራቅ ዘለግ ላሉ ቀናት መቆየት ተለማምደዋል።
በትንሽ ሽንቁር ውስጥ ራሳቸውን ያቆያሉ፣ በአልጋ ጠርዝ እጥፋት ውስጥ፣ ከመጋረጃ ሐዲድ ጀርባ ከፍተኛ የድብብቆሽ ጥበብ ራሳቸውን ያቆያሉ። የፀረ ተባይ መድኃኒቱ ርጭት ዋጋ ቢስ ከሆነ በኋላ ወጥተው ምግብ ይፈልጋሉ።
ትኋኖች ቆዳ ላይ ካረፉ በኋላ ለተወሰነ ጊዜ የቆዳ ቅኝት ያደርጋሉ። በቆዳ ሥር የሚገኝ የደም ማማለሻ (ካፒላሪስ) መስመር እስኪያገኙ ጥቂት ጊዜን ይሻሉ።
በመጀመሪያ ንክሻ ደም አያገኙም። ስለዚህ ደም ከሚወስዱበት አካል ደጋግመው ንክሻ ማድረግ አለባቸው።
ትኋንን ለማጥፋት ፍቱኑ መንገድ የቱ ነው?
በዓመታት የፀረ ተባይ መድኃኒት አልበግር እያላቸው ያሉት ትኋኖችን ለማጥፋት በርካታ ጥናቶችም ጥረቶች ተጀምረዋል።
ከቅርብ ጊዜ ወዲህ አንድ የተሻለ ነው የተባለው አዲስ መፍትሄ የኃያል ሙቀት ዘዴ ነው።
ትኋኖቹ አሉበት በሚባለው ክፍል ከፍ ያለ ሙቀት በመልቀቅ ማጥፋት ይቻላል።
በዚህ ዓመት በተደረገ ጥናት ተመራማሪዎች 5ሺህ 400 ለመራባት የደረሱ ትኋኖችን በናሙናነት የወሰዱ ሲሆን፣ ከ17 በፓሪስ ከሚገኙ አካባቢዎች ነው ትኋኖቹ የተለቀሙት።
እነዚህን ትኋኖች በአምስት ቡድን ከፋፍለው አስቀመጧቸው።
የተወሰኑትን ፍራሽ ጠርዝ፣ ሶፋ ሥር ወዘተ እንዲደበቁ አደረጉ። የተወሰኑትን ቡድኖች ደግሞ የተጋለጠ ሥፍራ እንዲሆኑ ተደረገ።
ከዚያ በክፍሎቹ ውስጥ ከፍ ያለ ሙቀት ተለቀቀ። ሙቀቱ 60 ዲግሪ ሴንቲግሬድ ነበር።
ከአንድ ሰዓት በኋላ አንድም በሕይወት የተረፈ ትኋን አልተገኘም።
ይህን ሙቀት መልቀቅ በቤት ውስጥ ማንም እንዲሞክረው የሚበረታታ አይደለም።
አንድ ባለሙያ ሰዎች ይህን ዘዴ እንዳይሞሩት ያስጠነቅቃሉ። “ይህ ዘዴ በጥናት ደረጃ ላይ ያለ ነው፤ በዚህ ሙቀት ቤት ለማሞቅ መሞከር ከትኋን ይልቅ ሰውን ያጠፋል፤ እሳት አደጋም ይፈጥራል” ይላሉ።
በ2021 የተደረገ አንድ ጥናት ግን ትኋኖች ሙቀት ሲለቀቅባቸው እንደሚሰደዱ አመላክቷል። በተለይም በአፓርትመንት ውስጥ የሚኖሩ ሰዎች ትልቁ ፈተና ትኋኖች ከአንድ ቤት ወደ ሌላው በቀላሉ መሸጋገር መቻላቸው ነው።
ሌላው ጥናት እንዴት ትኋኖችን ከተደበቁበት አባብሎ ማውጣት ይቻላል የሚል ነበር። አንድ በስቶክሆልም ሮያል ኢንስቲትዩት የተደረገ ጥናት አንድ መሣሪያ ፈጠረ።መሣሪያው የሰውን ትንፋሽ ሙቀት አስመስሎ የሚፈጥር ነው።
ማሽኑ የሰው እስትንፋስን አስመስሎ ካርቦንዳይኦክሳይድ ሲለቅ ትኋኖች ከያሉበት ተግተልትለው መውጣት ችለዋል።
ፈተና የሆነው ግን ከወጡ በኋላ በየትኛው የፀረ ተባይ መድኃኒት ይጠፋሉ የሚለው ነው። ብዙዎቹ የትኋን ዘርያዎች አሁን ያሉትን ፀረ ተባይ መድኃኒቶች ተላምደዋቸዋል።
በፈረንሳይ፣ በዩናይትድ ኪንግደም እና በአሜሪካ እነዚህ ትኋኖች ፈተና ሆነዋል።
ለመሆኑ የሰው ልጅ ከትኋን ጋር የገባውን ጦርነት ያሸንፍ ይሆን?
ተመራማሪው ዶ/ር በዝ “በፍጹም” ይላሉ። “የሰው ልጅ ከምድረ ገጽ ሲጠፋ ብቻ ነው ትኋን ከናካቴው ሊጠፋ የሚችለው።