‘ፈጣሪ፣ ሽጉጥ እና ትራምፕ’፡ ሺዎች የታደሙት የትራምፕ የምርጫ ቅስቀሳ

የፎቶው ባለመብት, EPA
ዶናልድ ትራምፕ ባሳላፍነው ሳምንት የካቴና ሲሳይ ይሆናሉ የሚሉ ወሬዎች ቢሰራጩም እሳቸው ግን ሺዎች በታደሙት ቅስቀሳ ላይ ተገኝተዋል።
በቴክሳስ ግዛት ዋኮ ከተማ በበርካታ ደጋፊዎቻቸው ፊት የተገኙት የቀድሞው ፕሬዝዳንት በኒው ዮርክ ከተማ የተከፈተባቸውን ምርመራ አጣጥለውታል።
የኒው ዮርኩ ምርመራ ዶናልድት ትራምፕ ለወሲብ ፊልም ተዋናይቷ ስቶርሚ ዳኒኤልስ ስለእሳቸው መረጃ እንዳታወጣ አፍ ማስያዣ ጉቦ ሰጥተዋል ይላል።
“መርማሪዎቹ እየመረመሩኝ ያሉት ወንጀል ሠርቼ አይደለም። ጥፋት አልፈፀምኩም። አሊያም ደግሞ አልማገጥኩም” ካሉ በኋላ በተዋንይቷ አቋም ቀልደዋል።
“በአገራችን ታሪክ እኔ በጣሙ የዋሁ ሰው ነኝ” ያሉት ዶናልድ መርማሪዎቹም ሁሉንም ነገር በርብረው ማስረጃ አለመግኝታቸውን ይናገራሉ።
ባለፈው ሳምንት ትራምፕ በቁጥጥር ሥር ከዋሉ በአገረ አሜሪካ “ሞት እና ጥፋት” ሊከተል እንደሚችል የሚያስጠነቅቅ መልዕክት ትሩዝ ሶሻል በተሰኘው የማኅበራዊ ሚዲያ ገፃቸው ላይ ሲጽፉ ነበር።
ነገር ግን በአሁኑ በቅስቀሳቸው ወቅት መሰል መልዕክት ያላቸውን ንግግሮች ከማስተላለፍ ተቆጥበዋል።
በሺዎች የሚቆጠሩ የቀድሞው ፕሬዝዳንት ደጋፊዎች ከቅስቀሳ ይልቅ ሕዝባዊ ክብረ-በዓል ስሜት ወዳለው አየር ማረፊያ አካባቢ ያለ ሜዳ መጥተው ሲበሉ፣ ሲጠጡ እንዲሁም ሲገበያዩ ውለዋል።
በርካቶች ‘ፈጣሪ፣ ሽጉጥ እና ትራምፕ’ አሊያም ‘ትራምፕ አሸንፈዋል’ የሚል ጽሑፍ ያለበት ቲሸርት ሸምተዋል።
በአባ፣ ፍራንክ ሲናትራ እና ቦን ጆቪ ሙዚቃዎች እየተዝናኑ የትራምፕን መምጣት በጉጉት ሲጠባበቁ የነበሩት ደጋፊዎች፣ የቀድሞው ፕሬዝዳንት ቀኝ እጅ የሆኑ ፖለቲከኞችን ንግግሮችን ሲያደምጡም ነበር።
የኮንግረስ አባላቱ ማት ጋየትዝ እና ማርጆሪ ቴይለር ግሪን፤ ዶናልድ ትራምፕ ላይ የተከፈተውን ምርመራ ሲያጣጥሉ ውለዋል።
አብዛኛዎቹ ፖለቲከኞች የኒው ዮርክ አካባቢ ዐቃቤ ሕግ የሆኑት አልቪን ብራግን በንግግራቸው ሲተቿቸው ነበር።
በሥፍራው የነበረው ሰው ብዛት 15 ሺህ ገደማ እንደሚሆን የትራምፕ ምርጫ ቅስቀሳ ሰዎች ይናገራሉ።
ሚድሎቲያን ከተሰኘች አነስተኛ ከተማ የመጣችው ዴቢ ሃርቪ “እኔ አሉታዊ ነገር አልሰማም” ትላለች። “እኔ ፀሎቴ ትራምፕ እንዳይታሰር ነው። ፈጣሪ አሁንም ፀሎት ይሰማል።”
ትራምፕን የሚያሞግሱ ቲሸርቶች የለበሱት ኖቪ እና ጓደኛው ሪቻርድ ታርነር፣ የዶናልድ ትራምፕን የምርጫ ቅስቀሳ ሲታደሙ ለመጀመሪያ ጊዜ ነው።
ምንም እንኳ ሌሎችም የሪፐብሊካን ዕጩዎች በ2024 ቢወዳደሩም እነሱ ግን ምርጫቸው ትራምፕ እንደሆነ ይናገራሉ።
“ሥራ መሥራት እንደሚችል አሳይቶናል” ይላል ታርነር፤ የትራምፕ ዋነኛ ተቀናቃኝ ሆነው የቀረቡት ፍሎሪዳው አገረ-ገዢ ሮን ዲሳንቲስን በሚወርፍ ንግግር።
የአሜሪካ መገናኛ ብዙኃን እና የዶናልድት ትራምፕ ተቺዎች የቀድሞው ፕሬዝዳንት በዋኮ ከተማ ቅስቀሳ ለማድረግ ለምን ፈለጉ ሲሉ ይጠይቃሉ።
ይህች ከተማ ከሰላሳ ዓመት በፊት ብራንች ዴቪዲያን የተሰኘ እምነት ተከታዮች ከፌዴራል እና ከግዛቲቱ ባለሥልጣናት ተጋጭተውባት 86 ሰዎችን አጥታለች።
ከተማዋ ለመንግሥት ባለሥልጣናት በለተይ ደግሞ ለፌዴራሉ መንግሥት ተወካዮች ቦታ የላትም።
በጉጉት ሲጠበቁ የነበሩት ትራምፕ በአዲሱ “ትራምፕ ፎርስ ዋን” አውሮፕላን እየከነፉ መጥተው በደጋፊዎቻቸው ጭብጨባና ጩኸት ታጅበው ወርደዋል።
ምንም እንኳ ፕሬዝዳንቱ ከተመረጡ ለአገራቸው አዲስ ሥራ ለመሥራት ቃል ቢገቡም፣ የቅስቀሳቸው ዋና አጀንዳ የነበረው ግን የምርመራው ጉዳይ ሆኖ ተገኝቷል።












