እናቱን የገደለው ካናዳዊ ተዋናይ የዕድሜ ልክ እስራት ተፈረደበት

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
ካናዳዊው ተዋናይ ራየን ግራንታም እናቱን በመግደሉ የዕድሜ ልክ እስራት ተፈረደበት።
ባርባራ ዋይት የተባሉትን እናቱን ከሁለት ዓመታት በፊት መግደሉን ፍርድ ቤት አስታውቋል።
የ24 ዓመቱ ተዋናይ ‘ሪቨርዴል’ በተሰኘው ታዋቂ የታዳጊዎች ተከታታይ ድራማ ላይ ጀፍሪ ኦገስቲን የተባለ ገጸ ባህሪ ወክሎ ይተውን ነበር ተብሏል።
ባለፈው ሳምንት ረቡዕ በቫንኩቨር ከተማ በሚገኘው የብሪትሽ ኮሎምቢያ ከፍተኛ ፍርድ ቤት ነው ውሳኔው የተላለፈው።
ተዋናዩ የግድያ ወንጀሉን መፈጸሙን ማመኑም ተገልጿል።
ዐቃቤ ሕግ እንዳለው የካናዳውን ጠቅላይ ሚኒስትር ጀስቲን ትሩዶ ለመግደልም ተዋናዩ ሲያሴር ነበር።
ተዋናዩ እናቱ ቫንኩቨር በሚገኘው ቤታቸው ፒያኖ እየተጫወቱ ሳለ ከኋላቸው ተኩሶ እንደገደላቸው አምኗል።
ተንቀሳቃሽ ስልኩ ላይ በቀረጸው ቪድዮ “ከኋላዋ ተኩሼ ጭንቅላቷን መታኋት። የተኮስኩት እኔ እንደሆንኩ አውቃ ነበር” ሲል ተደምጧል።
ከግድያው በኋላ ቢራ ጠጥቶና አደንዛዥ እጽ ተጠቅሞ ሦስት ሽጉጥ፣ ቤት ውስጥ የሠራውን ተቀጣጣይ፣ ደን ውስጥ ለመኖር ቆይታ የሚያስፈልግ ቁሳቁስ እና ወደ ጠቅላይ ሚኒስትር ጀስቲን ትሩዶ ቤት የሚወስድ ካርታ መኪና ውስጥ ይዞ ተገኝቷል።
ነገር ግን ከቤቱ ርቆ ወደ 200 ኪሎ ሜትር ገደማ መኪናውን ከነዳ በኋላ ወደ ቫንኩቨር ፖሊስ ጣቢያ ሄዶ “እናቴን ገደልኳት” ብሎ እጁን ሰጥቷል።
እጁን ከመስጠቱ በፊት ላየስን ጌት ብሪጅ ወይም ሳይመን ፍራሰር ዩኒቨርስቲ ሄዶ የጅምላ ግድያ የመፈጸም ዕቅድ እንደነበረውም ፖሊስ ገልጿል።
ሳይመን ፍራሰር ዩኒቨርስቲ ቀድሞ ተዋናዩ የተማረበት ነው።
ከልጅነቱ ጀምሮ በትወና የሚታወቀው ራየን፤ በ2019 ‘ሪቨርዴል’ ላይ ሲተውን ‘ሱፐርናቹናል’ በተባለው ተከታታይ ፊልምና ‘ዳያሪ ኦፍ ኤ ዊምፒ ኪድ’ በተባለው ፊልም ላይም ተውኗል።
ከታሰረበት ጊዜ አንስቶ የአእምሮ ጤና ክትልል እየተደረገለት እንደሆነ ፖሊስ ገልጿል።
በፍርድ ቤት ክርክር ወቅት የራየን ጠበቃ እንዳሉት፣ ራየን ጭንቀትና ድብታ ያሰቃየው ነበር። እናቱን ከመግደሉ ከወራት በፊት ሰዎችን የመግደል፣ ራሱንም የማጥፋት ፍላጎትም ነበረው ተብሏል።
ተዋናዩ ይግባኝ መጠየቅ የሚችለው ከተፈረደበት ብይን ውስጥ 14 ዓመቱን ከገባደደ በኋላ ነው።












