ዩኬ፣ ፈረንሳይ እና ጀርመን ኢራን ላይ የተጣለውን ማዕቀብ እንደማያነሱ ገለጹ

የኢራን ሚሳኤል

የፎቶው ባለመብት, REUTERS

ታትሟል

ዩናይትድ ኪንግደም፣ ፈረንሳይ እና ጀርመን ኢራን ላይ የተጣለውን የኒውክሌር ማዕቀብ እንደማያነሱ ገለጹ።

ማዕቀቡን የማያነሱት ኢራን ሰው አልባ አውሮፕላን (ድሮን) እና ሚሳኤል ለሩሲያ እንዳትሸጥ ጫና ለማሳደር ነው።

እአአ በ2015 ኢራን የኒውክሌር ስምምነት አድርጋ በምላሹ ማዕቀቦች እንዲነሱላት ተወስኖ የነበረ ሲሆን በስምምነቱ መሠረት የተወሰኑት ማዕቀቦች በቀጣዩ ወር ይነሳሉ ተብለው ነበር።

ሆኖም ሦስቱ አገራት እንደሚሉት ኢራን ዩራንየም በማከማቸትና በማበልጸግ ስምምነቱን ጥሳለች።

ኢራን የሦስቱ አገራት ውሳኔ ሕገ ወጥና ተንኳሽ ነው ስትል ምላሽ ሰጥታለች።

በከፍተኛ ደረጃ የበለጸገ ዩራኒየም የኒውክሌር መሣሪያ ለመሥራ ይውላል።

ቀነ ገደብ የሚያልፍበትን የተባበሩት መንግሥታት ማዕቀብ የሕጋቸው አካል እንደሚያደርጉ ሦስቱ አውሮፓውያን አገራት ገልጸዋል።

ኢራን ባለስቲክ ሚሳኤልና ድሮን እንዳትልክ ለማገድ ውሳኔው ቢተላለፍም ኢራን ለሩሲያ ድሮን ትልካለች። እነዚህም በዩክሬን ጦርነት ጥቅም ላይ ውለዋል ተብሎ ተገልጿል።

አሜሪካ፣ ዩኬ፣ ፈረንሳይ፣ ቻይና፣ ሩሲያ እና ጀርመን ከስምንት ዓመታት በፊት Joint Comprehensive Plan of Action (የጋራ አጠቃላይ የትግበራ ዕቅድ) JCPOA በሚል የጋራ ስምምነት ማድረጋቸው ይታወሳል።

ኢራን የኒውክሌር እንቅስቃሴ ልትቀንስና ዓለም አቀፍ ታዛቢ ልታስገባ ተስማምታ ነበር። በምላሹም ምጣኔ ሃብቷን ያሽመደመዱ ማዕቀቦች ሊነሱ ቃል ተገብቷል።

ስምምነቱ ማንም ድሮንና ሚሳኤል ለኢራን እንዳይሸጥ ወይም ከኢራን እንዳይገዛ አልያም እንዳያስተላልፍ ይከለክላል።

የኒውክሌር ሥራውን ይደግፋሉ የተባሉ ግለሰቦችና ተቋማት ንብረት ማዕቀብ እንዲጣልበትም ስምምነቱ ያዛል።

ከፊታችን ጥቅምት 18 (እአአ) በፊት ቻይና እና ሩሲያ እንደ ሦስቱ አውሮፓውያን አገራት ኢራን ላይ የተጣለውን ማዕቀብ አናነሳም እስካላሉ ድረስ በስምምነቱ ታሳሪ አይሆኑም ማለት ነው።

ኢ3 የሚባሉት ሦስቱ አውሮፓውያን አገራት ኢራን ስምምነቱን “ሙሉ በሙሉ ካልፈጸመች” ማዕቀብ እንደማያነሱ አስረግጠዋል።

ኢራን በበኩሏ ይህ ውሳኔያቸው ስምምነቱን እንዲሁም የተመድ የፀጥታው ምክር ቤት ውሳኔ ሐሳብ 2231 እንደሚጥስ ገልጻለች።

የቀድሞው የአሜሪካ ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ በ2018 አሜሪካን ከስምምነቱ ማስወጣታቸው አይዘነጋም።