አይኤስ ኢራቅ ድንበር አቅራቢያ 33 የሶሪያ ወታደሮችን ገደለ

IS

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

ታትሟል

እስላሚክ ስቴት (አይኤስ) ባሳለፍነው አርብ በሶሪያ ወታደሮች ላይ ለተፈጸመው ጥቃት ኃላፊነቱን ወሰደ።

አርብ ነሐሴ 5/2015 ዓ.ም. ከኢራቅ ድንበር አቅራቢያ በአውቶብሶች ሲጓዙ በነበሩ የሶሪያ ወታደሮች ላይ ጥቃት ተከፍቶ 33 ወታደሮች የተገደሉ ሲሆን 10 ሲቆስሉ 10 ወታደሮች ደግሞ አድራሻቸው ጠፍቷል።

መቀመጫውን በዩናይትድ ኪንግደም ያደረገው ሶሪያ ኦብዘርቫቶሪ ፎር ሂዩማን ራይትስ የተባለ የመብት ተሟጋች ቡድን የአይኤስ ታጣቂዎች ምስራቅ ሶሪያ ውስጥ በሁለት አውቶብሶች ሲጓዙ በነበሩ የአገሪቱ ወታደሮች ላይ ደንገተኛ ጥቃት ከፍቷል ብሏል።

33 ወታደሮች የተገደሉበት ይህ ጥቃት በዚህ ዓመት በአይኤስ የደረሰው ከፍተኛ ጥቃት ተብሎ ተመዝግቧል።

ቡድኑም በሁለት ወታደራዊ አውቶብሶች ላይ በከባድ ጦር መሳሪያዎች የታገዘ ጥቃት ከፍቶ አንዱን ተሸከርካሪ አቃጥሎ በርካታ ወታደሮችን መግደሉን ይፋ አድርጓል።

አይኤስ መሰል ጥቃቶችን አጠናክሬ እቀጥላለሁ ብሏል።

የሶሪያ ዜና ወኪል ሳና የአገሪቱን ጦር መኮንን ዋቢ አድርጎ “አሸባሪው” ቡድን ኢራቅ ድንበር አቅራቢያ በፈጸመው ጥቃት በርካታ የአገሪቱ ጦር አባላትን መግደሉን እና ማቁሰሉን ዘግቧል።

በዚህ ሳምንት መጀመሪያም የአይኤስ ጠንካራ ግዛት በሆነችው ራቃ 10 የሶሪያ መንግሥት ወታደሮች እና ለመንግሥት ወግኖ የሚዋጋ ቡድን አባላት በጽንፈኛ እስላማዊ ቡድኑ ተገድለው እንደነበረ መቀመጫውን በዩናይትድ ኪንግደም ያደረገው የመብት ተሟጋች ገልጿል።

በርካታ የኢራቅ እና ሶሪያ አካባቢን ይዞ የነበረው አይኤስ አሁን ድረስ ጠንካራ ይዞታዎቹ ናቸው ተብለው በሚገለጹት ራቃ እና ሃማ ግዛቶች ሰላማዊ ሰዎችን ጨምሮ 43 የመንግሥት ወታደሮችን በቅርብ ቀናት ገድሏል።

በተለይ ደግሞ ከቅርብ ወራት ወዲህ የአይኤስ ታጣቂዎች በሰሜን እና ሰሜን ምስራቅ ሶሪያ እየፈጸሙ ያሉትን ጥቃቶች ጨምረዋል።

አይኤስ በአንድ ወቅት ከሰሜን ምስራቅ ሶሪያ እስከ ሰሜን ኢራቅ ድረስ የተዘረጋ 88 ሺህ ስኩዌር ኪሎ ሜትር ቦታን ተቆጣጥሮ 8 ሚሊዮን በሚሆኑ ነዋሪዎች ላይ ካበድ የተባለ ሕግጋቱን ጥሎ ያስተዳድር ነበር።

ይሁን እንጂ ከእአአ 2019 ጀምሮ ቡድኑ በተወሰደበት እርምጃ ከፍተኛ ይዞታውን ተነጥቋል።

በቅርቡም የቡድኑ መሪ እንደሆነ የሚታመነው አቡ ሁሴን አል-ዉራይሺ በቱርክ ተገድሏል። የአይኤስ ወታደሮች አሁን ላይ ከሶሪያ በረሃዎች እየተነሱ ድንገተኛ ጥቃት ወደማድረስ የትግል ስልት ተቀይረዋል።

የተባበሩት መንግሥታት አሁንም ድረስ አይኤስ የደኅንነት አደጋ ነው ይላል።

የሶሪያ ፕሬዝዳንት በሽር አል-አሳድ በአገራቸው የተነሳውን የአረብ አብዮትን እአአ 2011 በኃይል ካስቆሙት በኋላ አገሪቱ ወደ እርስ በእርስ ጦርነት ገብታለች።

ግጭቱ ከጀመረ በኋላ ከግማሽ ሚሊዮን በላይ ሰዎችን የገደለ ሲሆን ከአጠቃላይ የአገሪቱ ሕዝብ ገሚሱን ከመኖሪያው አፈናቅሏል።