ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
ለሩስያ ሰልሏል የተባለ የጀርመን የደህንነት መስርያ ቤት ባልደረባ በአገር ክህደት ወንጀል ሊከሰስ ነው
የጀርመን ከፍተኛ ወታደራዊ መኮንን ለሩስያ ምስጢራዊ መረጃዎችን አሳልፎ በመስጠት በአገር ክህደት ወንጀል ሊከሰስ ነው።
ካርስተን ኤል በዩክሬን እየተካሄደ ስለሚገኘው ጦርነት እንዲሁም ስለ ዋግነር ቡድን ወታደራዊ ምስጢሮችን ለሩስያ አሳልፎ መስጠቱን እና ለዚህም ተግባሩ 400 ሺህ ዩሮ እንደተከፈለው የአቃቤ ሕግ መረጃ ያስረዳል።
ሌላ መረጃውን በማቀባበል የተጠረጠረ ጀርመናዊ ነጋዴም አብሮ መከሰሱ ተገልጿል።
ሁለቱም ጀርመናውያን ጥፋተኛ ሆነው ከተገኙ የእድሜ ልክ እስራት ይጠብቃቸዋል ተብሏል።
የጀመርን የደህንነት መስርያ ቤት ባልደረባ የሆነው እና ካርስተን ኤል የተባለው ግለሰብ በአንድ ክፍል ውስጥ ከባህርማዶ የሚደወሉ ስልኮችን እና የኢንተርኔት ልውውጦችን መከታተል የስራ ድርሻ ነበረው ተብሏል።
ግለሰቡ በቁጥጥር ስር ከመዋሉ ጥቂት ቀናት ቀደም ብሎ የሰዎችን የጀርባ ታሪክ የሚያጣራው ክፍል እድገት አግኝቶ ተዛውሮ አንደነበር የመገናኛ ብዙኀን ዘገባ ያስረዳል።
ካርስተን ኤል በቁጥጥር ስር የዋለው ባለፈው ዓመት ሕዳር ወር ላይ ነው።
ከአንድ ወር በኋላም ተባባሪ ነው የተባለውን አርተር ኢ ከአሜሪካ ወደ ጀርመን ሲመጣ አውሮፕላን ማረፍያ ላይ በቁጥጥር ስር ውሏል።
አርተር ኢ ጀርመናዊ የንግድ ሰው ቢሆንም የተወለደው ሩስያ ሲሆን ወደ ሞስኮ በመሄድ ለሩስያ የአገር ውስጥ ደህንነት ሰዎች መረጃውን ማቀበሉ ተጠርጥሯል።
ሁለቱም ግለሰቦች “በአገር ክህደት ወንጀል” እንደሚከሰሱ አቃቤ ሕግ ገልጿል።
አሁን የሚጠበቀው በርሊን የሚገኝ ችሎት ጉዳያቸውን ለማየት እና ላለማየት የሚሰጠው ውሳኔ ነው።
ጀርመናዊው ነጋዴ በእንቁ ንግድ ላይ የተሰማራ መሆኑ በቁጥጥር ስር ከዋለ በኋላ ተገልጿል።
ሁለቱ ግለሰቦች ለመጀመርያ ጊዜ የተገናኙት እኤአ በ2021 ባቫርያ ውስጥ በሚገኝ አንድ የእግር ኳስ ክለብ ውስጥ ነው።
የአቃቤ ሕግ ቢሮ በሁለቱ ግለሰቦች ላይ ስለተመሰረተው ክስ ተጠይቆ አስተያየት ከመስጠት ተቆጥቧል።
ሩስያ ዩክሬን ላይ ጦርነት ከከፈተች በኋላ በአውሮጳ ስለላዎችን ታደርጋለች የሚል ስጋት እና ጥርጣሬ እያየለ መጥቷል።
ዩኬ፣ ፖላንድ እና ኖርዌይ የሩስያ ሰላዮች ናቸው ያሏቸውን በቁጥጥር ስር አውለዋል አልያም ከአገራቸው ለቅቀው እንዲወጡ አድርገዋል።
ባለፈው ወር በጀርመን ከጦር መሳርያዎች ጋር የተያያዘ ስራ የሚሰራ ግለሰብ በስለላ ተጠርጥሮ በቁጥጥር ስር ውሏል።
የጀርመን ሳይበር ሴኪውሪቲ ኃላፊ ከሩሲያ ደህንነት መስርያ ቤት ጋር ግንኙነት ካላቸው ሰዎች ጋር ቅርበት አለው በሚል ከስራ ገበታው ላይ ተሰናብቷል።