ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
ትዊተር ‘ለሰማያዊ ጭረት’ ስምንት ዶላር የሚያስከፍልበትን አሠራር በድጋሚ ጀመረ
ለተወሰነ ጊዜ ተቋርጦ የነበረው ‘ለሰማያዊ ጭረት’ [ብሉ ቲክ] ስምንት ዶላር የሚያስከፍለው የትዊተር አሠራር በድጋሚ ተጀመረ።
‘ሰማያዊ ጭረት’ በሚያጭበረብሩ የትዊተር ተጠቃሚዎች ምክንያት አሠራሩ ባለፈው ወር ተቋርጦ ነበር።
በአፕል ኤሌክትሮኒክሶች ትዊተርን የሚጠቀሙ ሰዎች 10 ዶላር ሲከፍሉ የተቀረው ተጠቃሚ ስምንት ዶላር የሚከፍል ይሆናል።
የትዊተር ባለቤት ኤሎን መስክ አፕል ከተጠቃሚዎቹ ተጨማሪ ክፍያ ስለሚጠይቅ ለአፕል ተጠቃሚዎች ትዊተር የሚጠይቀው ክፍያ መጨመሩን ገልጿል።
ትዊተር በጽሑፎች ላይ አርትኦት ማድረግ የሚያስችል አሠራርም ዘርግቷል።
የትዊተር ተጠቃሚዎች አሠራሩ እንዲዘረጋ ሲጠይቁ ነበር። ይህ አሠራር የሐሰተኛ መረጃ ስርጭትን ያባብሳል ብለው የሚሰጉም አሉ።
የተጠቃሚዎች ትክክለኛ ማንነት ማረጋገጫ የሆነውን ‘ሰማያዊ ጭረት’ የሚጠቀሙ ሰዎች በትዊተር የሚያዩት የማስታወቂያ መጠን ይገደባል።
ዝነኛ የትዊተር ተጠቃሚዎችን ለመለየት የሚውለው ይህ ምልክት ከዚህ ቀደም የሚሰጠው በነጻ ነበር።
ከዚህ በኋላ ግን ከንግድ ጋር የተያያዙ ገጾች ወርቃማ ጭረት ሲሰጣቸው ሌሎች ተጽዕኖ ፈጣሪዎች ግራጫ ጭረት ይኖራቸዋል።
ስማቸውን የሚቀይሩ ወይም የገጽ ምሥል የሚያሳዩ ተጠቃሚዎች ሰማያዊ ጭረታቸውን ይዘው የሚቀጥሉት ትዊተር ክለሳ ካደረገ በኋላ እንደሆነ ተገልጿል።
ትዊተር ለማረጋገጫው ጭረት ስምንት ዶላር አስከፍላለሁ ሲል፣ ብዙ የገጹ ተጠቃሚዎች ታዋቂ ሰዎችን በማስመሰል ሰማያዊ ጭረት ሲጠቀሙ ነበር። ኤሎን መስክን አስመለስለው ገጽ የከፈቱም ነበሩ።
መስክ ትዊተርን በ44 ቢሊዮን ዶላር ከገዛ በኋላ በርካታ ለውጦች አምጥቷል።
ድርጅቱ በቀን አራት ሚሊዮን ዶላር እየከሰረ በመሆኑ ትርፋማ የሚያደርጉት አሠራሮች መዘርጋት እንዳለበት ገልጿል።
ከድርጀቱ ሠራተኞች ግማሽ ያህሉ ተባረዋል። ዘለግ ያለ የሥራ ሰዓት ስለሚኖርም በትዊተር ዋና ቅርንጫፍ ለሠራተኞች ማረፊያ አልጋ ገብቷል።
ዶናልድ ትራም እና ካንዬ ዌስት ገጻቸው ከተሰረዙባቸው መካከል ይጠቀሳሉ። ለተወሰነ ጊዜ ጥቅም ላይ ያልዋሉ ገጾች እንደሚሰረዙ ትዊተር ገልጿል።
በዚህ አሠራር ከዚህ ዓለም በሞት የተለዩ ሰዎች ገጽ ሊሰረዝ መቻሉ የብዙዎችን ልብ ሰብሯል።