የአሜሪካ ደኅንነት 'ዩፎዎችን' በተመለከተ የሰበሰበውን መረጃ በይፋ አስታወቀ

ታትሟል

ምንነታቸው ያልታወቀ በራሪ አካላት በእንግሊዘኛው [Unidentified Flying Objects] ወይም ዩፎዎችን በተመለከተ አሜሪካ በ50 ዓመታት ለመጀመሪያ ጊዜ ለሕዝብ ክፍት የሆነ የምክር ቤት ውይይት አካሂዳለች።

ዩፎዎች ታይተው እንደሆነ እንዲያጣሩ ሁለት ከፍተኛ ወታደራዊ ባለሥልጣኖችን ኃላፊነት ተሰጥቷቸው ነበር።

ይህ ኃላፊነት የተሰጣቸው ሁለት ከፍተኛ መኮንኖች እንዳሉት፣ ዩፎዎች ታይተው እንደሆነ ለመፈተሽ ቢሞከርም ማረጋገጫ ለማግኘት የተደረገው ጥረት ብዙ መሰናክሎች ገጥመውታል።

ሕዝብ በቀጥታ እንዲከታተል ክፍት የተደረገው የምክር ቤት ውይይት፣ ስለ ዩፎዎች ለሚነሱ ጥያቄዎች ይህ ነው ሊባል የሚችል ተጨባጭ መልስ አልሰጠም።

ንግግር ያደረጉት ሁለቱ የአሜሪካ መኮንኖች፣ ዩፎዎችን በአውሮፕላን ለመቃኘት የተደረገው ጥረት 11 ጊዜ ጫፍ ደርሶ ነበር ብለዋል።

በምክር ቤቱ ምን ተባ?

በምክር ቤቱ የአሜሪካ የጸረ ሽብር ኃይል ወኪል፣ የደኅንነት ክፍል ወኪል እንዲሁም የፔንታገን ስለላ አመራር ሮናልድ ሞልትሬ ተገኝተዋል።

"ጥልቅ" ምርምር ከተደረገ የዩፎዎችን እንቅስቃሴ ሙሉ ለሙሉ ባይሆንም መቃኘት እንደሚቻል የሚጠቁም መረጃ ሰጥተዋል።

"ማንኛውም የምናየው ቁስ ሊለይ፣ ሊጠና ይችላል። አስፈላጊ ሆኖ ከተገኘም ይወገዳል" ብለዋል ሮናልድ ሞልትሬ።

ከዚህ ቀደም ይህ ነው ሊባል የሚችል ማብራሪያ የሌላቸው ክስተቶች አጋጥመዋል።

ለምሳሌ እአአ በ2004 ላይ የአሜሪካ ተዋጊ አውሮፕላን አብራሪዎች ፓሲፊክ አካባቢ ሰማይ ላይ ያዩት ተጠቃሽ ነው።

አብራሪዎቹ በራሪ አካሉ በአስር ሺዎች የሚቆጠር ጫማ ዝቅ ካለ ቆሞ ተሽከርክሯል።

ሌላኛው ክስተት ለመጀመሪያ ጊዜ ለሕዝብ ይፋ የተደረገው በምክር ቤቱ ውይይት ወቅት ነው።

ንብረትነታቸው የአሜሪካ የባሕር ኃይል የሆነ ተዋጊ ጀቶችን አንዳች በራራዊ አልፎ ሲበር ይታያል።

ይህ ቁስ ምን እንደሆነ ግን አልታወቀም።

የባሕር ኃይል ደኅንነት ምክትል ኃላፊ ስኮት ብሬይ "አሁን ባለን መረጃ ልናብራራቸው የማንችል የተወሰኑ ክስሰቶች አሉ። እኛ ማወቅ የምንፈልገውም እነዚህን ነው" ብለዋል።

ምንነታቸው ያልታወቀ በራሪ አካላት ከምድራችን ውጭ ካሉ ዓለሞች (extra-terrestrial aliens) የመጡ ሊሆኑ ይችላሉ የሚለውን በተመለከተ ጥርጣሬ እንዳላቸው ተናግረዋል።

ከሌሎች ዓለሞች የመጡ ተፈጥሯዊም ይሁን ኢ-ተፈጥሯዊ የሆነ ባህሪ ያላቸውና ያልታወቁ ቁሶች ከዚህ ቀደም እንዳልተገኙ በማስረጃነት ጠቅሰዋል።

ከእነዚህ ቁሶች ጋር ግንኙነት ለመፍጠር ተሞክሮ እንደማያውቅም አስረድተዋል።

"ምንነታቸው ያልታወቀ በራሪ አካላትን በተመለከተ ባደረግነው ምርመራ ከሌላ ዓለም የመጡ ስለመሆናቸው የሚጠቁም መረጃ አላገኘንም" ብለዋል።

ዩፎዎች የደኅንነት ስጋት ናቸው?

በምክር ቤቱ ቃላቸውን የሰጡ ሕግ አውጭዎች እንዳሉት፣ ምንነታቸው ያልታወቁ የትኛውም አይነት በራሪ አካላት ለብሔራዊ ደኅንነት ስጋት ናቸው።

የሪፐብሊካን ፓርቲ አባሉ ሪክ ክሮፎርድ፣ ለደኅንነት አስጊ ስለሆነ ቁስ ዝርዝር መረጃ አለመኖሩ "አስጊ ስለሆነ መፍትሄ ያሻናል" ሲሉ አቋማቸውን ገልጸዋል።

የባሕር ኃይል ደኅንነት ምክትል ኃላፊ ስኮት ብሬይ እንዳሉት፣ ምንነታቸው ያልታወቀ በራሪ አካላትን መፍጠር የሚችል ቴክኖሎጂ ያላቸው አገሮች ስለመኖራቸው አሜሪካ አታውቅም።

ዩፎዎች ለምን አነጋጋሪ ሆኑ?

በሰማይ የሚታዩ ብርሃን አመንጭ በራሪ አካላትን በተመለከተ ለዓመታት ጥያቄዎች ተሰምተዋል። በርካቶች በዝርዝር ማወቅ ከሚፈልጓቸው ጉዳዮች አንዱም ነው።

አሜሪካ ውስጥ ለሕዝብ ይፋ የሆነ የምክር ቤት ውይይት ለመጨረሻ ጊዜ የተካሄደው በ1966 ነበር።

በወቅቱ የያኔው የሪፓብሊካን ፓርቲ አባልና ኋላ ላይም ፕሬዝዳንት ጀራልድ ፎርድ ስለ ዩፎዎች በይፋ ውይይት እንዲደረግ አስችለዋል።

ይህ ውይይት የተካሄደው ሚሺጋን ውስጥ ፖሊሶችን ጨምሮ ከ40 በላይ ሰዎች ምንነታቸው ያልታወቀ በራሪ አካላት ማየታቸውን ተከትሎ ነው።

የአገሪቱ የአየር ኃይል ክስተቱ የኬሚካሎች ድብልቅ የፈጠረውን ጭስ ተከትሎ የተፈጠረ ነው ቢልም፣ ጀራልድ ፎርድ ግን ክስተቱን በአግባቡ የሚያስረዳ ምላሽ እንዲሰጥ ጫና አሳድረዋል።

በ1969 በአየር ኃይል የተካሄደ 'ብሉ ቡክ' የተባለ ምርመራ ምንነታቸው ያልታወቀ በራሪ አካላት ለአሜሪካ ብሔራዊ ደኅንነት አስጊ አይደሉም ሲል ደምድሟል።

በ2017 ግን ጉዳዩ ዳግመኛ ለውይይት ተከፈተ።

በወቅቱ ፔንታጎን ዩፎዎች አይተናል ብለው ሪፖርት ካደረጉ አውሮፕላን አብራሪዎች እና የአሜሪካ መከላከያ አባላት በሚስጥር መረጃ መሰብሰብ መጀመሩ ነበር ጉደዮን አነጋጋሪ ያደረገው።

ዩፎዎችን የሚያሳዩ ተንቀሳቃሽ ምሥሎች በሪፖርቱ ተካተዋል። ዩፎዎቹ በማይጠበቅ ሁኔታ እንደሚበሩ፣ ከፍተኛ ንፋስ ሲነሳ አንድ አካባቢ እንደሚደርሱ እና የሚበሩበትን ፍጥነት በድንገት እንደሚለዋውጡ ተጠቁሟል።

አውሮፕላን አብራሪዎች ዩፎዎቹን በወታደራዊ ቢሮዎች አቅራቢያ "በየቀኑ እናያቸው ነበር" ብለዋል።

አንድ መረጃ አጋላጭ እንዳሉት፣ ዩፎዎች የአሜሪካን የኒውክሌር መሣሪያ የሚያውክ እንቅስቃሴ አድርገዋል። ይህም መሣሪያዎቹን ከኢንተርኔት ትስስር ማስወጣትን ያካትታል።

በ2020 የቀድሞው ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ለኮሮናቫይረስ መከላከያ ከመደቡት ገንዘብ የተወሰነው የአሜሪካ የስለላ ተቋማት ስለ ዩፎዎች የሰበሰቡትን መረጃ በ180 ቀናት ውስጥ ይፋ እንዲያደርጉ የዋለ እንደነበር ይታወሳል።

በ2021 ሰኔ ላይ የአሜሪካ ብሔራዊ ስለላ ተቋም ኃላፊ እንደገለጹት፣ በ144 አጋጣሚዎች የታዩ ምንነታቸው ያልታወቀ አካላትን በተመለከተ ዝርዝር መረጃ አልተገኘም።

እነዚህ አካላት መታየታቸው የተነገረው በ2004 ሲሆን፣ እንደ ፊኛ ያለ ቅርጸ እንዳላቸው የመሰከሩ ነበሩ።

ይህንን በተመለከተ የወጣው ሪፖርት፣ ምንነታቸው ያልታወቀው አካላት ሥሪታቸው አንዳች ቁስ ይመስላል ለማለት እንደሚቸግር ይጠቁማል።

ከታዩት አካላት ወደ 80 የሚጠጉትን መቃኘት የተቻለው እጅግ በተራቀቁ ወታደራዊ መነጽሮች ነው።

ምን እንደሆኑ፣ እንዴት እንደሚንቀሳቀሱ ስላልታወቀ ተጨማሪ ምርምር እንዲደግ ሐሳብ ቀርቧል።

ባለፈው ኅዳር በፕሬዝዳንት ጆ ባይደን የተፈረመ ሕግ፣ ማንኛውም ዓይነት መረጃ ሲገኝ በይፋ እንዲገለጽ ግዴታ ይጥላል።

የአሜሪካ መከላከያ ስለ ዩፎዎች የሚያጠና የምርምር ቡድን በይፋ እንዲያቋቁም ሕጉ ያስገድዳል።