ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
የቀድሞ የኒሳን ሃላፊን ያስመለጡት አባት እና ልጅ ለጃፓን ተላልፈው ተሰጡ
የቀድሞ የኒሳን ሃላፊን ያስመለጡት አባት እና ልጅ ለጃፓን ተላልፈው ተሰጡ
የቀድሞ የኒሳን ሃላፊ ከጃፓን እንዲያመልጡ ረድተዋል የተባሉት አሜሪካውያኑ አባት እና ልጅ ለጃፓን መንግሥት ተላልፈው ተሰጡ።
በምዝበራ ወንጀል በጃፓን መንግሥት የሚፈለጉት የቀድሞ የኒሳን ዋና ሥራ አስኪያጅ ካርሎስ ግሆሰን በሳጥን ውስጥ ተደብቀው በግል አውሮፕላን እንዲያመልጡ ረድተዋል የተባሉት አባት እና ልጅ በአሜሪካ በቁጥጥር ሥር ውለው ለወራት ቆይተዋል።
ማይክል ታይለር እና ልጁ ፒተር ታይለር ተላልፎ ላለመሰጠት ለወራት ሲከራከሩ ቢቆዩም፤ ትናንት ለፓጃን መንግስት ተላልፈው መሰጠታቸውን ጠበቆቻቸው አስታውቀዋል።
ዐቃቤ ሕግ እንደሚለው አባት እና ልጅ የቀድሞውን የኒሳን አለቃ ከጃፓን እንዲወጣ በማገዛቸው 1.3 ሚሊዮን ዶላር ተከፍሏቸዋል።
የ60 ዓመቱ አባት ማይክል ታይለር ጡረታ ከመውጣቱ በፊት በአሜሪካ ጦር ውስጥ የልዩ ጦር አባል ነበር። ከዚህ በተጨማሪም በውጪ አገራት በአስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ የሚገኙ ሰዎችን የሚያስመልጥ የአሜሪካ መንግሥት ድርጅትን ይመራ እንደነበረ ተነግሯል።
ቫኒቲ ፌይር የተሰኘው መጽሄት አባት እና ልጅ ከ20 በላይ በአስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ የነበሩ ሰዎችን ከተለያዩ አገራት ማስመለጣቸውን እና ለዚህም ለእያንዳንዱ ሥራ ከ20ሺህ እስከ 2 ሚሊዮን የአሜሪካ ዶላር ድረስ ለአገልግሎታቸው ከፍያ መቀበላቸውን ያትታል።
ካርሎስ ጎህሰን በዝርዝር በተጠና እና በረቀቀ መልኩ ከቶኪዮ አምልጠው ከጃፓን መንግሥት ጋር የተፈላጊ ሰዎች ልውውጥ ስምምነት ወደሌላት ሌባኖስ ቤይሩት ገብተዋል።
በብራዚል የተወለዱት ካርሎስ ጎህሰን የብራዚል እና ሌባኖስ ጥምር ዜግነት አላቸው። የልጅነት ጊዜያቸውንም በሌባኖስ አሳልፈዋል።
የጃፓኑ ኤንኤችኬ ቴሌቪዥን ጣቢያ ካርሎስ ጎህሰን በቁም እስር ከነበሩበት መኖሪያ ቤት ተነስተው በአቅራቢያቸው ወደሚገኝ ሆቴል ሲገቡ ያሚያሳይ የሲሲቲቪ ምስል አስመልክቶ ነበር።
ከዚያም ጎህሰን በሆቴሉ ከሁለት ሰዎች ጋር ከተገናኙ በኋላ፤ ባቡር ተሳፍረው ወደ ወደ ጃፓኗ ኦሳካ ከተማ ተጉዘዋል።
ከኦሳካ ፍተሻ ባልተደረገበት ጥቁር ሳጥን ውስጥ ተደብቀው በግል ጄት ተሳፍረው ከጃፓን ሳይወጡ እንደማይቀር ይገመታል።
የቀድሞውን የኒሳን አለቃ የያዘችው አውሮፕላን ከጃፓን ተነስታ በቱርክ አድርጋ ሌባኖስ አርፋለች።
ቱርክ ባሳለፍነው ወር ግለሰቡ ከጃፓን እንዲያመልጡ ረድተዋል ያለቻቸውን ሁለት አብራሪዎች እና የአየር መንገድ ሥራ አስኪያጅ ጥፋተኛ ብላ በእስር እንዲቀጡ ወስናለች።
ካርሎስ ጎህሰን የመኪና አምራቸን ኩባንያውን ገንዘብ መዝብረዋል በሚል እአአ 2018 ላይ በቁጥጥር ሥር ከዋሉ በኋላ ወራቶችን በእስር ቤት እና በመኖሪያ ቤታቸው የቁም እስረኛ በመሆን አሳልፈዋል።
በመኖሪያ ቤታቸው የ24 ሰዓት ክትትል እየተደረገባቸው እያለ ነው ማምለጥ የቻሉት።
ጎህሰን ከጃፓን ካመለጡ በኋላ በሌባኖስ መግለጫ በሰጡበት ወቅት የኒሳን ኩባንያ አለቃ ሳሉ ምንም አለማጥፋታቸውን ገልፀው የቀረበባቸውን ክስ አጣጥለውም ነበር።